#ሱባዔና_ሥርዓቱ
እንኳን ለጾመ ፍልሰታ ለማርያም አደረሳችሁ!!!
ሱባዔ በሰዋስው ትርጉሙ ሰባት ማለት ነው፡፡ ሱባዔ በመንፈሳዊ አተረጓጎም አንድ ሰው ከዚህ ቀን እስከዚህ ቀን በጸሎት ከፈጣሪዬ እገናኛለሁ ብሎ የሚያቅደው መንፈሳዊ ዕቅድ ነው፡፡ ሰባት ቁጥር በእስራኤላውያን ዘንድ በሥራም በቃልም የሚገለጥ ፍጹም ቁጥር ነው፡፡ ለምሳሌ፡- ፈጣሬ ዓለማት እግዚአብሔር በሰባተኛው ቀን ሥነ ፍጥረትን ከመፍጠር ማረፉ፣ ለጸሎት የሚተጉ ምእመናን
በቀን ለሰባት ጊዜ ማመስገናቸው የሰባት ቁጥርን ፍጹምነት ያመለክታል፡፡ ዘፍ.2፥2፤ መዝ.118፥64፡፡ ከዚህ አንጻር አንድ ሰው ለሰባት ቀናት ቢጾም አንድ ሱባዔ ጾመ ይባላል፡፡ ለዐሥራ አራት ቀን ቢጾም ሁለት ሱባዔ ጾመ እያለ እየጨመረ ይሄዳል፡፡
#መቼ_ተጀመረ?
ሱባዔ የተጀመረው ከውድቀት በኋላ በመጀመሪያው ሰው በአዳም ነው፡፡ ቅዱሳን መላእክት አዳምን ጸሎት መጸለይን እንዳስተማሩት የመጽሐፍ ቅዱስ ሊቃውንት ይናገራሉ፡፡መላእክት ለአዳም ጊዜያትን አስተምረውት ነበር፡፡ ቅዳሴ ማርያም ትርጓሜ፡፡ አዳም ጥፋቱን አምኖ ከባሕር ውስጥ ሱባዔ በመግባቱና በመጸለዩ እግዚአብሔር በማይታበል ቃሉ ከአምስት ቀን ተኩል በኋላ ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንኀለሁ ሲል ቃል ኪዳን ገብቶለታል /መጽሐፈ ቀሌምጦስ አንቀጽ አራት/፡፡
#ሱባዔ_ለምን?
የሰው ልጅ ኃጢአት በሚስማማው የሥጋ ሰውነቱ ዘወትር ፈጣሪውን ይበድላል፡፡ በፈጸመው በደል ኅሊናው ይወቅሰዋል፡፡ ይጸጸታል፡፡ በመጀመሪያ ደፍሮ በሠራው ኃጢአት በኋላ ይደነግጣል፡፡ ይህ በማንኛውም ሰብአዊ ፍጥረት ኅሊና ውስጥ የሚፈራረቅ ክስተት ነው፡፡ በዚህ ጊዜ የፈጣሪውን ይቅርታ ለማግኘት ያስባል፤ ይተክዛል፡፡በውስጡ ሰውነቴ በእግዚአብሔር ሕግ ደስ ይለኛል. ነገር ግን በብልቶቼ ባለ በኃጢአት ሕግ የሚማርከኝ ሌላ ሕግ አያለሁ፡፡ እኔ ምንኛ ጐስቋላ ሰው ነኝ ለዚህ ሞት ከተሰጠ ሰውነት ማን ያድነኛል? እንዳለ ቅዱስ ጳውሎስ፡፡ ሮሜ.7.22-25፡፡
ሰው በደፋርነቱ የኃያሉን አምላክ ትእዛዝ ተላልፎ ትካዜ ሽክም ሲያስጨንቀው ሸክሙን የሚያቃልልበትና የሚያስወግድበት መንፈሳዊ ጥበብ ከቸሩ ፈጣሪ ተሰጥቶታል፡፡ ይኸውም በጥቂት ድካመ ሥጋ ጸጋ እግዚአብሔር የሚያገኝበት ሥርዓት ሱባዔ ነው፡፡ ከጥንት እስከ ዛሬ አንድ ሰው በትካዜ ሸክም መንፈሱ ሲታወክ የነፍስና የሥጋ ጸጥታውን ለመመለስና ለማስከበር መጾምና መጸለይ ግድ ይሆንበታል፡፡ በዚህ ጊዜ አመክሮ /ሱባዔ/ ይገባል፡፡
#እግዚአብሔርን_ለመማፀን
ሰው ሱባዔ ከሚገባባቸው መሠረታዊ ጉዳዮች አንዱ እግዚአብሔርን ለመማፀን ነው፡፡ ማንኛውም ሰው ሱባዔ ሲገባ በቁርጥ ወደ ፈጣሪው የሚያቀርበው ተማኅፅኖ ሊኖረው ይገባል፡፡ ምንም የምንጠይቀው /የምንማፀነው/ ነገር ሳይኖር ሱባዔ ብንገባ የምናገኘው መልስ አይኖርም፡፡ ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታና ዝግጅት ሱባዔ የሚገቡ ሰዎች ከሱባዔ በኋላ ምን እንደ ተመለሰላቸው የሚያውቁት ነገር ስለማይኖር ሱባዔ በመግባታቸው የሚያገኙት ነገር የለም፡፡
ስለዚህ ሱባዔ ከመግባታችን በፊት፡- ሱባዔ የምገባው ለምንድን ነው? በማለት ራሳችንን መጠየቅ ይኖርብናል፡፡ ለምሳሌ አንድ ክርስቲያን በግል ሕይወቱ ዙሪያ ስለ ሀገር ሰላም፣ ስለ ጓደኛው ጤና ወዘተ ጉዳዮች ላይ ፈጣሪውን ይማፀናል፡፡ በዚህ ጊዜ በግል ሕይወቱም ሆነ በሀገር ጉዳይ ለገባው ሱባዔ ወዲያውኑ መልስ ሊያገኝ ይችላል፤ እንዲሁም መልሱ ሊዘገይ ይችላል፡፡ በዚህ ጊዜ ከተሐራሚው ትዕግሥት /መታገሥ/ ይጠበቅበታል፤ «ለምን ላቀረብኩት ጥያቄ ቶሎ መልስ አልተሰጠኝ?» በማለት ማማረርና እግዚአብሔርን መፈታተን ተገቢ አይደለም፡፡ እግዚአብሔር ሥራውን የሚሠራበትና ለሚማፀነውም መልስ የሚሰጥበት የራሱ ጊዜ አለው፡፡ ለምሳሌ በጓደኛው ውድቀት ምክንያት ሱባዔ ገብቶ በአንድ ሳምንት ውስጥ መልስ ያገኘ የአንድ ገዳም አገልጋይ ታሪክ መመልከት ተገቢ ነው፡፡
አኃው ለተልእኮ በወጡበት አንዱን ድቀት አግኝቶት አድሯል፡፡ በነጋው ወንድሜ እኔ ድቀት አግኝቶኛልና እንግዲህ ወዲህ ተመልሼ ከዚያ ገዳም አልሔድም፤ ሽለሙን መስዬ እኖራለሁ አለው፡፡እኔም እንጂ አግኝቶኛል፤ ይልቁንስ ሔደን ኃጢአታችንን ለመምህረ ንስሐችን ነግረን፤ ቀኖናችንን ተቀብለን እንደ ቀደመው ኾነን እንኖራለን ብሎ አጽናንቶ ይዞት ሔደ፡፡ ሔደው ለመምህረ ንስሐቸው ነግረው ቀኖናቸውን ተቀብለው 1 /አንድ/ ሱባዔ፣ ቀኖና እንዳደረሱ ሰረይኩ ለከ በእንተ ዘኢገብረ እኁከል፤ ኃጢአት ስላላደረገው ወንድምህ ይቅር ብዬሃለሁ የሚል ድምፅ አሰምቶታል፡፡ /ዜና አበው/፡፡
ከላይ ታሪካቸው የሰፈረው የገዳም አገልጋዮች ለአገልግሎት በተላኩበት አገር አንዱ ድቀት አግኝቶት በዝሙት ሲወድቅ ጓደኛው እንደ እርሱ ድቀት እንዳገኘው አድርጐ ጓደኛውን በማጽናናት ወደ ገዳም በመመለስ አንድነት ኾነው ሱባዔ ይገባሉ፡፡ አንድ ሱባዔ /ሰባት ቀን/ እንደ ጨረሱ ከእግዚአብሔር ዘንድ ኃጢአት ሳይሠራ ለአንተ ብሎ ሱባዔ ስለገባው ወንድምህ ስል ይቅር ብዬሃለሁ የሚል ፈጣን መልስ አግኝቷል፡፡ ስለዚህ ሱባዔ በግል ሕይወትም ሆነ በጓደኛችን ሕይወት ዙሪያ ስንገባ ፈጣን ወይም የዘገየ መልስ ሊሰጠን ስለሚችል በትዕግሥት መጠባበቅ ይኖርብናል፡፡
#የቅዱሳንን_በረከት_ለመሳተፍ
ቅዱሳን አባቶችና ቅዱሳት እናቶች የተጋደሉትን ተጋድሎ በማዘከር ቃል ኪዳን በተሰጣቸው ገዳማትና አድባራት የሚገባ ሱባዔ የቅዱሳኑን በረከት ተካፋይ ያደርጋል፡፡ ቅዱሳን በሚጋደሉበት ቦታ ከወንዶችና ከሴቶች ልጆች ይልቅ የሚበልጥ ስም እሰጣቸዋለሁ፤ የማይጠፋ የዘላለም ስም እሰጣቸዋለሁ /ኢሳ.56.6/ በማለት እግዚአብሔር ቃል ኪዳን ስለ ገባላቸው ሱባዔ በመግባት በረከታቸውን መሳተፍ ይቻላል፡፡ በጾመ ነቢያት የነቢያትን በረከት ለመሳተፍ፣ በጾመ ሐዋርያት የሐዋርያትን በረከት ለመሳተፍ፣ በጾመ ፍልሰታ የእመቤታችንን በረከት ለመሳተፍ ሱባዔ መግባት የነበረና ወደ ፊትም የሚኖር የቤተ ክርስቲያን ሥርዓት ነው፡፡ ዛሬ ይህን ሥርዓት በመከተል የተለያዩ ቅዱሳንን በረከት ለመቀበል /ለመሳተፍ/ የቅዱሳን አፅም ካረፈበት ገዳም በጾም፣ በጸሎት፣ በጉልበትም ገዳማትን በማገልገል የቅዱሳንን በረከት ደጅ የሚጠኑ ምእመናንና መናንያን በየገዳማቱ እጅግ በርካታ ናቸው፡፡
ይኸውም በመጽሐፈ ነገሥት ካልዕ በምዕራፍ 2.9 እንደ ተመለከተው ነቢዩ ኤልሳዕ መምህሩን ኤልያስን በማገልገል የኤልያስ በረከት በእጥፉ በኤልሳዕ ላይ አድሮበታል፡፡ ይህን አብነት በማድረግ በየገዳማቱ በትህርምት የሚኖሩ መናንያንን ያገለገሉበትን ገዳም አባት በረከት በእጥፍ እየተቀበሉ ለሌሎችም የሚያቀብሉ አባቶች በየገዳማቱ አሉ፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ ሆኖ በስመ ገዳማዊ የምእመናንን ገንዘብ የሚዘርፉና የእውነተኛ መነኮሳትንና መናንያንን የተቀደሰ ሕይወት የሚያጐድፉ መኖራቸውን መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡
#የተሰወረ_ምሥጢር_እንዲገለጥልን
በዘመነ ብሉይ እግዚአብሔር ለአንዳንድ ነገሥታት ራእይ በማሳየት ምሥጢርን ይሰውርባቸው ነበር፡፡ ለምሳሌ የግብፁን ፈርዖን፣ የባቢሎኑን ናቡከደነፆርንና ብልጣሶርን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ዘፍ.41.14-36፡፡ ዳን.4.9፤ ዳን.5.4፡፡ እነዚህ ነገሥታት በግል ሕይወታቸውም ሆነ በመላው ሽክም ወደ ፊት ሊፈጸም የሚችል ራእይ ቢያዩም ቅሉ ራእዩን በትክክል ተረድተው እንዲህ ይሆናል የማለት ብቃት አልነበራቸውም፡፡ ስለዚህ በዘመናቸው ይኖር የነበሩትን ነቢያት ሱባዔ ገብተው የሕልማቸውን ትርጉም እንዲነግሩአቸው ይማፀኑ ነበር፡፡ ነቢያትም ሱባዔ በመግባት ነገሥታቱ ያዩትን የምሥጢረ ሥጋዌ ነገርና የመንግሥታቸውን አወዳዳቅ ገልጸው
አሸናፊ ሰጠ (Ashenafi Teshome), [10/08/2022 12:36 pm]
ይናገሩ ነበር፡፡ ዳን.5.28፡፡
እንዲሁም ቅዱሳን በየራሳቸው ያዩት ራእይ ምሥጢር ሲከደንባቸው የራእዩ ምሥጢርና ትርጉም እንዲገለጥላቸው ሱባዔ ይገባሉ፡፡ እግዚአብሔርም በንጽሕና ሆነው የገቡትን ሱባዔ ተመልክቶ ምሥጢር ይገልጥላቸዋል፡፡ ለምሳሌ ነቢዩ ዕዝራ የመጻሕፍትን ምሥጢር እንዲገልጥለት ሱባዔ ቢገባ የጠፉትን የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ዳግም መልሶ ለመጻፍ ችሏል፡፡ መዝ.8.1፡፡
#የሱባዔ_ዓይነቶች
#የግል_ ሱባዔ/ዝግ ሱባዔ/
የግል ሱባዔ አንድ ሰው ብቻውን ሆኖ በቤትና በአመቺ ቦታ የሚይዘው ማንም ሰው ሳያየው በግሉ የጸሎት በኣቱን ዘግቶ በሰቂለ ኅሊና ሆኖ ፈጣሪው ብቻ እንዲያየው እንዲሰማው በኅቡዕ የሚፈጽመው ሱባዔ ነው፡፡ ማቴ.6፡5-13፡፡ በዚህ ዓይነት መልክ አንድ ሰው ሱባዔ ሲገባ ዘጋ ይባላል፡፡ ዝግ ሱባዔ የያዘ ሰው የሚያስፈልገውን ነገር ይዞ ወደ በኣቱ ከተከተተ በኋላ ሱባዔው እስኪፈጸም ድረስ ከሰው አይገናኝም፡፡ መዝ. 101-6-7፡፡
#የማኅበር_ሱባዔ
የማኅበር ሱባዔ የሚባለው ካህናት፣ ምእመናን ወንዶችና ሴቶች፣ ሽማግሌዎችና ወጣቶች በአንድ ሆነው በቤተ ክርስቲያንና አመቺ በሆኑ ቦታዎች ሁሉ ተሰብስበው የሚገቡት ሱባዔ ነው፡፡ በብሉይ ኪዳን የነበሩ ምእመናን ወደ እግዚአብሔር በመሄድ ይጸልዩ ነበር፡፡ 1ኛ ሳሙ.1፡9፤ መዝ.121፡1፤ ሉቃ.18፡10-14፡፡
በሐዲስ ኪዳንም የሐዋርያት ተከታዮች የኾኑ መነኮሳት፣ ካህናትና ምእመናን በገዳማት፣ በአድባራት፣ የሰንበት ት/ቤት ተማሪዎች፣ የጽዋ ማኅበርተኞች ስለ ማኅበራቸው ጥንካሬና ከማኅበርተኞቹ መካከል አንዱ ችግር ሲገጥመው የማኅበር ሱባኤ ይያዛል፡፡.
#የዐዋጅ_ሱባዔ
የዐዋጅ ሱባዔ በአገር ላይ ድንገተኛ አደጋ፣ አባር ቸነፈርና ጦርነት ሲከሰት እንዲሁም ለማኅበረ ምእመናን አስጊ የሆነ መቅሰፍት ሲከሰት፣ እግዚአብሔር መዓቱን በምሕረት ቁጣውን በትዕግሥት እንዲመልስ የሚያዝ የሱባዔ ዓይነት ነው፡፡ ለዚህ ዓይነቱ ሱባዔ የነነዌ ሰዎችና በፋርስ በስደት ይኖር የነበረ እስራኤላውያን ተጠቃሾች ናቸው፡፡ የነነዌ ሰዎች የዮናስን ስብከት ሰምተው ከሊቅ እስከ ደቂቅ ለሦስት ቀን ከመብል ከመጠጥ ተከልክለው በመጾም በመጸለይ እግዚአብሔር መዓቱን በምሕረት ቁጣውን በትዕግሥት እንዲመልስ አድርገዋል፡፡ ሌላው በፋርስ በስደት ይኖር የነበረ አይሁድ በአስቴር ትእዛዝ የያዙት ሱባዔ ተጠቃሽ ነው፡፡ በዚያን ዘመን አርጤክስስ አይሁድ በያሉበት እንዲገደሉ በማዘዙ ከዚህ የጅምላ ጭፍጨፋ ለመዳን አይሁድ በዐዋጅ ሱባዔ ገብተዋል፡፡ አስቴር ገብታ ንጉሡን ስታናግረው ሌላው ሕዝብ በውጭ ዐዋጅ ዐውጀው ሱባዔ ገብተው ፈጣሪያቸውን ተማፅነዋል፡፡ አስቴር 4፡16 – 28፡፡
በአገራችንም ይህን የመሰለ የዐዋጅ ሱባዔ በዐፄ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት ተደርጓል፡፡ ፋሽስት ጣልያን አገራችንን በመውረር ኢትዮጵያን ቅኝ ተገዥ ለማድረግ ድንበሯን አልፎ በመጣበት ወቅት ንጉሠ ነገሥት ምኒልክ፡-ጉልበት ያለህ በጉልበትህ ጉልበት የሌለህ በጸሎትህ ርዳኝ በማለት የዐዋጅ ሱባዔ መያዛቸው ይነገራል፡፡ በዚህም መሠረት በየገዳማቱ ምሕላ ተይዟል፤ ንጉሡም ታቦተ ጊዮርጊስን ይዘው ዓለምን እጅግ ያስደነቀ ጥቁሮችን ለነጻነታቸው እንዲነሣሱ የሚያስችል ፋና ወጊ የሆነ ድል አግኝተው አገራችንን ለቅኝ ግዛት ያሰበውን ፋሽስት ጣልያንን ማሸነፋቸው በከፍተኛ ስሜት የምናስታውሰው ነው፡፡
#ቅድመ_ዝግጅት
ሱባዔ መግባት የሚፈልግ ምእመን ቅድመ ዝግጅት ማድረግ ይኖርበታል፡፡ ያለምንም ዝግጅት ሱባዔ መግባት ለፈተና ያጋልጣል፡፡ ስለዚህ ቅድመ ሱባዔ /ሱባዔ ከመግባት አስቀድሞ/፣ ጊዜ ሱባዔ/ በሱባዔ ጊዜና ድኅረ ሱባዔ /ከሱባዔ በኋላ/ ዝግጅት አስፈላጊ ነው፡፡
#ቅድመ_ሱባዔ /ሱባዔ ከመግባት አስቀድሞ/
በመጀመሪያ ሱባዔ የምንገባበትን ምክንያት ለይቶ ማወቅ ያስፈልጋል፡፡ አንድ ሰው ሱባዔ የሚገባበትን ዓላማ ለይቶ ካስቀመጠ ከሱባዔ በኋላ የሚጠበቀውን ነገር ማግኘት አለማግኘቱን ይረዳል፡፡ ይህ ሳይሆን ሱባኤ ቢገባ ከሱባኤው በኋላ የጠየቀው ነገር ስለሌለ ትርጉም ያጣል፡፡ ስለዚህ ሱባዔ ከመግባታችን በፊት ለምን ሱባኤ ለመግባት እንዳሰብን ለይተን ማወቅ ይኖርብናል፡፡
ሱባዔ ለመግባት የወሰንበትን ምክንያት ከለየን በኋላ ምክንያታችንን ይዘን የንስሐ አባታችንን ማማከር ያስፈልጋል፡፡ ምክንያቱም በምክረ ካህን መጓዝ መጀመር ክርስቲያናዊ ግዴታ ነው፡፡ ከዚህ ባሻገር በአባትነታቸውና በሕይወት ልምዳቸው ምን ማድረግ እንደሚገባን ምክር ለማግኘት እገዛ ያደርግልናል፡፡ ቅድመ ሱባኤ ከንስሐ አባት ጋር መመካከር ተገቢ ይሆናል፡፡ ለምሳሌ አንድ ሰው በሱባዔ ወቅት የተለያዩ ፈተናዎች ቢያጋጥሙት የተሰጠውን ምክር በመጠቀም ፈተናውን ለመቋቋም ይችላል፡፡ እንዲሁም የንስሐ አባቱ በሱባዔ ወቅት በጸሎት እንዲያስቡት መማከር የራሱ የሆነ ድርሻ አለው፡፡
ሱባዔ ለመግባት ስናስብ ለምን ያህል ቀናት መቆየት እንዳለብን መወሰን ያስፈልጋል፡፡ ሱባዔ ከዚህ እስከዚህ እቆያለሁ ብለን ዕቅድ የምንይዝበት ነው፡፡ እንደ አቅማችንና እንደ ችሎታችን ከዚህ ቀን እስከዚህ ብለን በመወሰን ሱባዔ መግባት ተገቢ ይሆናል፡፡ ለምሳሌ፡- ምንም ዓይነት ልምድ ሳይኖረው አንድ ሰው በዋሻ እዘጋለሁ ቢል ከጥቅሙ ጉዳቱ ሊያመዝን ይችላል፡፡ ምክንያቱም በሱባዔ ወቅት ፈተና ስለሚበዛ የሚመጣበትን ፈተና መቋቋም ባለመቻል ሱባዔው ሊቋረጥ ይችላል፡፡ ስለዚህ ቅድመ ሱባዔ ዐቅምንና ችሎታን አገናዝቦ መወሰን ተገቢ ነው፡፡
ሌላው ቅድመ ሱባዔ ለሱባዔ ተስማሚ የሆነ ወቅትና ቦታ መምረጥ ተገቢ ነው፡፡ በቤተ ክርስቲያን በአብዛኛው ሱባዔ የሚገባው አጽዋማትን ተከትሎ ነው፡፡ ስለዚህ ሱባዔ የምንገባበት ወቅት የጾም ወቅት መሆን አለመሆኑን መለየት ያስፈልጋል፡፡ በአጽዋማት ወቅት የሚያዝ ሱባዔ ለተሐራሚ ጠቀሜታው እጅግ የጐላ ነው፡፡ ምክንያቱም በአጽዋማት ወቅት ብዙ አባቶች ሱባዔ ስለሚይዙ ከአባቶች ጸሎት ጋር ልመናችንና ጸሎታችን ሊያርግ ይችላል፡፡ ስለዚህ ወቅትን ለይቶ ማወቅ ያስፈልጋል፡፡
እዚህ ላይ ከወርኃ አጽዋማት ውጭ ሱባዔ አይያዝም የሚል አቋም ለመያዝ አይደለም፡፡ አንድ ሰው ፈተና ከአጋጠመው በማንኛውም ጊዜ ሱባዔ ሊገባ እንደሚችል እዚህ ላይ ለመጠቆም እንወዳለን፡፡ ከዚህም ባሻገር ሱባዔ የምንይዝበትን ቦታ መምረጥ አለብን፡፡ ለሱባዔ የምንመርጣቸው ቦታዎች ለፈተና የሚያጋልጡ መሆናቸውን ማረጋገጥ ያስፈልጋል፡፡ ይኸውም ሱባዔ ከተገባ በኋላ ኅሊናችን እንዳይበተን እገዛ ያደርግ ልናል፡፡ ጫጫታና ግርግር የሚበዛበት ቦታ በሰቂለ ኅሊና ለመጸለይ አያመችም፡፡ ስለዚህ ሱባዔ የምንይዝባቸው ቦታዎች ከከተማ ራቅ ያሉ ገዳማትና አድባራት ተመራጭ ናቸው፡፡
#ጊዜ_ሱባዔ_/በሱባዔ_ጊዜ/
በጸሎት ሰዓት ዓምድና ግድግዳ ሳይደገፉ መቋሚያ ሳይዙ በሁለት እግር ቀጥ ብሎ በመቆም መጸለይ ይኖርብናል፡፡ እንዲሁም ፊትን ወደ ምሥራቅ መልሶ መቆም ወዲያና ወዲህ ወደ ግራ ወደ ቀኝ አለመዟዟር በሰፊሐ እድ በሰቂለ ኅሊና ኾኖ መጸለይ ይገባል፡፡ መዝ.5፡3፤ መዝ.133፡2፤ ዮሐ.11፡41፡፡
በመጨረሻም ሱባዔ የገባ ሰው ሱባዔውን ሳይጨርስ ወይም ሱባዔውን አቋርጦ ከማንም ሰው ጋር ፈጽሞ መገናኘት የለበትም፡፡
#ድኅረ_ሱባዔ_/ከሱባዔ በኋላ/
ለቀረበ ተማኅፅኖ እግዚአብሔር የሚያደርግልንን ነገር መጠበቅ ይኖርብናል፡፡ እግዚአብሔር ላቀረብንለት ምልጃና ጸሎት እንደ ልባችን መሻት እንደ እርሱ ቸርነት እርሱ በወደደ ጊዜ ያደርግልናል፡፡ ከሱባዔ በኋላ መጀመሪያ የምናገኘው የህሊና ሰላምን ነው፡፡ ይህ ትልቅ የአምላክ ስጦታ ነው፡፡ ከዚህ ባሻገር ሱባዔ ገብተን ያሰብነውን ካላገኘን ዳግመኛ ተዘጋጅተን እስከ መጨረሻው ሰዓት መማፀን መጽናት ይኖርብናል፡፡ መልካም የሱባዔ ጊዜ ይሁንልን፡፡
ምንጭ:- www.eotcmk.org/a/ሱባዔና-ሥርዓቱ-2/
Comments powered by CComment