ወደምስራቅ ተመልከቱ
በቅዳሴ መሀል ወደ ምስራቅ ተመልከቱ ሲባል ምን እናስተውል?
አብያተ ክርስቲያናት የሚገነቡት ፊታቸውን ወደ ምሥራቅ አዙረው ነው፡፡እኛም የምንጸልየው ፊታችንን ወደ ምሥራቅ አዙረን ነው፡፡ምክንያቱም ምሥራቅ ለኛ ብዙ ክስተቶችን ያስታውሰናል ፡፡ምሥራቅ በእግዚአብሔር ዘንድ የተመረጠ ሆኖ እናገኘዋለን ፡፡ስለዚህ እኛም ለምሥራቅ አስፈላጊውን ክብር መስጠት ይገባናልና ወደ ምሥራቅ ተመልከቱ ብሎ ዲያቆኑ በቅዳሴ መሀል ያነቃናል፡፡ምክንያቱም

1ኛ እግዚአብሔር ሰውን ከመፍጠሩ በፊት ለርሱ የብርሃን መውጫ ይሆንለት ዘንድ ምሥራቅን ፈጠረለት፡፡እግዚአብሔርም ብርሃኑ ጥሩ እንደሆነ አየ፡፡፡ከዚያም በአራተኛው ቀን ፀሐይን ፈጠረ፡፡ሰውን ደግሞ በስድስተኛው ቀን ፈጠረ፡፡ዘፍ ፩፡፳፮ የፀሐይ መውጣት የክርስቶስ ብርሃን ምሳሌ ነው፡፡ስለ ጌታ የፅድቅ ፀሐይ ትወጣላችሗለች ፈውስም በክንፎቿ ውስጥ ይሆናል ፡፡እናንተም ትወጣላችሁ እንደ ሰባም እንቦሳ ትፈነጫላችሁ፡፡ሚል ፬፡፪ ተብሎ ተጽፏል፡፡ስለዚህ ሚልክያስ በትንቢቱ የተናገረለት የጽድቅ፡ብርሃን የሆነ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ (እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ ")እንዳለ ሰው ሆኖ ተገልጦ በብርሃኑ ጨለማችንን ማራቁን እንድናስብ ማንቃቱ ነው፡፡
2ኛ. እግዚአብሔር ሰውን ከመፍጠሩ በፊት በምሥራቅ በዔደን ገነትን ተከለ፡፡ሰውንም በዚያ አስቀመጠው የሕይወትንም ዛፍ በኤደን ተከለ ዘፍ ፪፥፰ የዔደን ገነትም ተስፋ የምናደርጋት የመንግስተ ሰማያት(የኢየሩሳሌም ሰማያዊት) ምሳሌ ናት፡፡ሰውም ፊቱን ወደ ምሥራቅ አዙሮ ሲጸልይ የገነትን የሕይወት ዛፍ ምኞቱን ይገልጻል ያ በገነት የነበረው የሕይወት ዛፍ አዳም ሕጉን ጠብቆ ለ አንድ ሺ አመት ቢቆይ ኖሮ ከዚህች የሕይወት ዛፍ ተመግቦ ተሀድሶን አግኝቶ ህግ ካለበት(ይህንን ብላ ይህንን ደግሞ አትብላ)ተብሎ ከታዘዘበት ከገነት ወጥቶ ሕግ ወደ ሌለበት ቅዱስ ፣ቅዱስ፣ቅዱስ ብሎ ማመስገኑ መብል መጠጥ ረፍት ክብር ሆኖት ወደሚኖርበት ወደ መንግሥተ ሰማያት ይገባ እንደነበር እናንተም በሃይማኖት ሆናችሁ በምግባር ጸንታችሁ የዘላለም ሕይወት የሚሆነውን የጌታችንን ሥጋና ደም እየተቀበላችሁ ብትኖሩ መንግስተ ሰማያት የሚያስገባችሁ መሆኑን አትዘንጉ ሲል ነው ፡፡
3ኛ.ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተወለደው በምሥራቃዊት ሐገር ነው፡፡ሰብአሰገልም ኮከቡም የወጣው ከምሥራቅ ነው ማቴ ፪፥፪ ምክንያቱም ሰብአ ሰገል ሲከተሉት ወደ ጌታ መርቷቸዋልና ኮከቡ የመለኮት መምራት ምሳሌ ነው፡፡ ስለዚህ ዲያቆኑ ውስተ ጽባሕ ነጽሩ ሲል አምላካችን ስለኛ ሲል ትስብዕትን መዋሀዱን በጨርቅ መጠቅለሉን በከብቶች በረት መወለዱን አስቡ ሲለን ነው፡፡
4ኛ.እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በምሥራቅ ባለው ደጅ ትመሰላለች "ወደ ምሥራቅ ወደሚመለከተው በስተውጭ ወደአለው ወደ መቅደሱ በር አመጣኝ ተዘግቶም ነበር ፡፡እግዚአብሔርም ይህ በር ተዘግቶ ይኖራል እንጂ አይከፈትም ሰውም አይገባበትም፡፡የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ገብቶበታልና ተዘግቶ ይኖራል፡፡ሕዝ ፵፬፥፩-፪ ይላል ፡፡ አንድም የፀሐይ መውጫ ምሥራቅ ነው። በዚህም መሰረት ፀሐይ የጌታችን የፀሐዩ መውጫ ምሥራቅ ደግሞ የእመቤታችን ምሳሌ ስለሆነ ዲያቆኑ ውስተ ጽባሕ ነጽሩ ሲል ከምስራቋ ከእመቤታችንና ከልጇ ከጌታችን ጋር እንዳላችሁ በእምነት አስተውሉ ሲለን ነው፡፡
5ኛ.ጌታችን አምላካችን በምሥራቃዊት ሀገር ተሰቀለ ፡፡ለዓለም ኃጢአት ሥርየት ይሆን ዘንድ ደሙን በምሥራቃዊት ሐገር አፈሰሰ፡፡ድኅነትም ወደ ዓለም በምሥራቅ በኩል መጣ፡፡አሁንም እኛ ወደ ምሥራቅ መመልከታችን አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ በምሥራቅ ሀገር ባፈሰሰው ደሙ በቆረሰው ሥጋው ማዳኑን እያሰባችሁ በርሱ በኩል የተሰጣችሁንን ድኅነት በኃይማኖት ሆናችሁ በምግባር ጸንታችሁ እየጠበቃችሁ መሆናችሁን ራሳችሁን መርምሩ ሲለን ነው፡፡
6ኛ. ኢየሩሳሌም በምሥራቅ ነች እርሷም የታላቁ ንጉሥ የመድኃኔ ዓለም ሀገር ነች፡፡ክርስትናና ቤተ ክርስቲያንም በምሥራቃዊት ሐገር በኢየሩሳሌም ተጀመሩ ፡፡ወንጌልም ከምስራቅ ለዓለም ሁሉ ተሰራጨ የመጀመሪያውም የክርስቲያን ሰማዕት ደም በዚያ ፈሰሰ፡፡ስለዚህ ወደምሥራቅ እንድናይ በታዘዝን ጊዜ አምላካችንን ኢየሱስ ክርስቶስን በልባችን አንግሠን ማለት "ልጄ ሆይ ልብህን ስጠኝ" ምሳ ፳፫፥፳፮ያለውን ቃል አስበን ልቡናችንን ለክርስቶስ ማደሪያነት ሰጥተን "እግዚአብሔር ለሕዝቡ በመጽሐፍ ይናገራል " መዝ ፹፯፥፮ እንደተባለ ጌታችን በሥጋ ተገልጦ እንድንፈጽም ያዘዘንን የወንጌል ቃል ለመፈጸም ጣሩ፡፡ሐዋርያቱ አርድዕቱ ወንጌልን ለማስተማር እንደተጉ እናንተም ወንጌልን ለማስተማር ትጉ፡በዚሁ በምሥራቅ ቅዱስ እስጢፋኖስ የወንጌልን ቃል ሲመሰክር በድንጋይ ተወግሮ እንደሞተ እናንተም የወንጌሉን ቃል ለማድረስ ስትሉ የሚመጣባችሁን መከራ ሁሉ በአኮቴት ለመቀበል ዝግጁዎች ሁኑ ሲለን ነው፡፡
7ኛ.መጽሐፍ ቅዱስ ምሥራቅን ብዙ ጊዜ የእግዚአብሔር ክብር መሆኑን ገልጿልና "ስለዚህ እግዚአብሔርን በምሥራቅ የእስራኤልንም አምላክ የእግዚአብሔርንም ስም በባሕር ደሴቶች አክብሩ፡፡ኢሣ ፳፬፥፲፭ ተብሎ ተጽፏል፡፡በሕዝቅኤል መጽሐፍም ክርስቶስ በክብር ከምሥራቅ እንደሚመጣ "እነሆ የእሥራኤል አምላክ ክብር ከምስራቅ መንገድ መጣ፡፡ድምጹም እንደ ብዙ ውኆች ይተምም ነበር፡፡በክብሩ ምድር ታበራ ነበር፡"ሕዝ፵፫፥፫ተብሎ ተተንብዮአል፡፡ስለዚህ ወደ ምሥራቅ ተመልከቱ ባለ ጊዜ እግዚአብሔር ክብሩን እንዲያሳያችሁ ና ክብሩን እንዲያጎናጽፋችሁ በመሻት ሆናችሁ ቁሙ ሲለን ነው፡፡
8ኛ.ወደ ምሥራቅ ስንመለከት በምሥራቅ ያለውን መሰዊያ እናያለን መስዋዕቱም ፋሲካችን ክርስቶስ ነው፡፡እርሱም መስዋዕት የሆነው በምሥራቅ ነው፡፡ስለዚህ ወደ ምሥራቅ ተመልከቱ ሲል አምላካችሁ ስለ እናንተ መስዋዕት ሆኖ መቅረቡን አስቡ ሲለን ነው፡፡
9ኛ.የነገረ መለኮት ሊቃውንት የክርስቶስ ዳግም ምጽአት በምሥራቅ ይሆናል ይላሉ፡፡ምክንያቱም "ወደ ሰማይ እንደ ሄደ ሁሉ እንዲሁ ይመጣልና "ሐዋ ፩፥፲፩ የተባለው በኢየሩሳሌም መሆኑና በዘካርያስ ትንቢትም በዚያ ቀን እግሮቹ በኢየሩሳሌም ትይዩ በምሥራቅ በኩል ባለው በደብረ ዘይት ላይ ይቆማሉ ዘካ ፲፬፥፬ ተብሎ ተጽፏልና፡፡ዳግም ለፍርድ መምጣቱን እያሰባችሁ ተዘጋጅታችሁ ጠብቁት ሲለን ነው፡፡
10ኛ..በጥምቀት ተጠማቂውና የክርስትና አባቱ ወይም እናቱ ወደ ምሥራቅ ይመለከታሉ ፡፡የሃይማኖትንም ጸሎት በመጸለይ ሰይጣንን እንደማያመልኩት ያረጋግጣሉ፡፡ስለዚህም ተጠማቂው ከምዕራብ ወደ ምሥራቅ እንደተሸጋገረ ይሰማዋል፡፡ያም ከጨለማ ወደ ሚደነቅ ብርሃን መሸጋገር ነው፡፡ስለዚህ ወደ ምሥራቅ ተመልከቱ ባለ ጊዜ ጌታችን በከፈለልን ካሳና በመሠረተልን ጥምቀት ከሲኦል ወጥታችሁ ወደ ገነት መግባታችሁን አስባችሁ ድኅነታችሁን ለመፈፀም ልጅነታችሁን አፅንታችሁ ያዙ ሲለን ነው፡፡
ይቆየን

Comments powered by CComment