በስመአብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሀዱ አምላክ::

‘ቤተክርስቲያናችን ተማሪ አስተምሪ      አንድነት ስላሉሽ መሪና ተመሪ ‘  

በዋግ ኽምራ ሀገረ ስብከት ወለህ ደብረገነት ቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያን ልማት ኮሚቴ

1 መግቢያ
"ተሰአሎ ለአቡከ ወይነግረከ ወለሊቃውንቲከ ይዜንዉከ፤

አባትህን፡ጠይቅ፡ይነግርሃል፤ሊቃውንትህንጠይቅይነግሩህማል፡፡"ዘዳ.32፤7

ወላጅ አባት ለልጅ እያበላ እያጠጣ እያለበሰ እየጠበቀ ያሳድገዋል፡፡ ለዕድሜና ለአእምሮው እየመጠነም የሚጠቅመውንና የሚጐዳውን እንዲለይ ያስረዳዋል፡፡ ስለዚህም አዲስ ነገር ሲገጥመው አባቱን ይጠይቃል፡፡
በመንፈሳዊ ሕይወትም እንዲሁ ነው፡፡ በቀለምና በቃለ እግዚአብሔር የሚወልዱን መምህራን አባቶች ይባላሉ፡፡ ስለዚህም ነው ነቢየ እግዚአብሔር ሙሴ “አባትህን ጠይቅ ይነግርሃል፤ ሊቃውንትህን ያስረዱሃል” የሚለው፡፡ ለመጠየቅ ግን መጀመሪያ የሚጠየቁት መኖር አለባቸው፡፡ የሚጠየቅ ከሌለ መጠየቅ የሚፈልግስ ማንን ሊጠይቅ ይችላል ?
የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ተጠያቂዎች ሊቃውንት መገኛ ምንጮች ደግሞ የአብነት ትምህርት ቤቶች ናቸው፡፡ ትምህርት ቤቶች በሚገባቸው መጠን ካሉ አበው ሊቃውንትን በማፍራት ለአባትነት መዓርግ አብቅተው ይሰጡናል፡፡ ያን ጊዜ እኛ መጠየቅ እንችላለን፤ የምንፈልገውንም ምግብና /መንፈሳዊ ጸጋ/አግኝተን በነፍስ በስጋ እንለመልማለን፡፡ በተለይ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን አብነት ትምህርት ቤቶች ለረጅም ዘመናት የሶስቱም ዘርፎች መሪዎች መገኛ ምንጮች ነበሩ፡፡

የቤተ መንግስት ሰራተኞቹ ሕዝቡን ለማስተዳደር የሚረዳውን ዕውቀት ሌላው ቢቀር ማንበብና መጻፋን የሚማሩት ከመምህራነ-ቤተ ክርስቲያን ነበር፡፡ ቤተ ክርስቲያንንም የሚመሩት አባቶችና ተጠያቂ ዓይናማ ሊቃውንት ምንጫቸው እነዚሁ ት/ቤቶች ነበሩ፡፡ ሶስተኛዎቹ  ደግሞ ቅዱሳን ናቸው፡፡ ገቢረ-ተአምራትንና ሐዋርያነትን ገንዘብ አድርገው  በመከራ ተፈትነው በገድል ተቀጥቅጠው ቅዱሳን የምንላቸው የአባቶች ምንጭም እነዚሁ ትምህርት ቤቶች ናቸው፡፡ ስለዚህ ትምህርት ቤቶችን መጠበቅ ሁሉንም ዓይነት ሰዎች ለማግኘት መጋደል ነው፡፡
በአሁኑ ጊዜ የአብነት ት/ቤቶች ያሉበት ሁኔታ ግን አሳዛኝ ነው፡፡ መምህራኑ የሚበሉት የሚለብሱት የላቸውም፤ ደቀመዛሙርትም ቁራሽ የሚሰጣቸው አጥተዋል፡፡ ስለዚህ ግሮቹን ፈትቶ ት/ቤቶችን ማቆየት፤ ሲቻል ደግሞ ዘለቄታዊ መፍትሔ በማምጣት ለሀገሪቱ የሚያበረክቱትን አስተዋጽኦ ማጐልበትና ዓለም አቀፋዊ ዕውቅና እንዲኖራቸው ማድረግ ከዚህ ትውልድ  የሚጠበቅ ነው፡፡

ለኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን መስፋፋትም የሚያስብ ካለ የትኩረት ቦታውን ከአብነት ት/ቤቶች ሊያርቅ አይገባውም፡፡ -ሐዋርያዊነትን ገንዘብ ያደረጉ ደቀ-መዛሙርት እንዴት ይፈጠራሉ?ተመሳስለውና ሰርገው በመግባት ቤተ ክርስቲያኒቱን ለማጥቃት  የተነሱ  ሃይሎችን እንዴት መግታት ይቻላል? በቤተ ክርስቲያናችን የተከማቸው የብዙ ዘመን ሀብት ከትውልዱ እንዴት ይደርሳል?” የሚል ካለ ዓይኑን ወደ አብነት ት/ቤቶች ማንሳት ይኖርበታል፡፡

ት/ቤቶቹ ላይ መሰራት የሚገባው ስራ በርግጥ ቀላል አይደለም::ሕልውናቸው እንዳይጠፋ መታደግ የመጀመርያው ይሁን እንጂ የምንፈልገውን ለማግኘት ግን ብዙ መስራትና ብዙ ምዕራፎችን መሻገርንም ይጠይቃል:: ከእነዚህም አንዱና ዋናው በተጠና መንገድ ችግሮቻቸውን ለመፍታት መንቀሳቀስ ነው::
በዚሁ መሰረት የወለህ ደብረ-ገነት ቅድስት ማርያም ቤተ-ክርስቲያን የአብነት ት/ቤትን ግንባታ እውን ለማድረግ ይህ ፕሮጀክት ተዘጋጅቷል፡፡

Comments powered by CComment